EAR

አዲስ ነገር

Wednesday, 9 January 2019

ስለ ወያኔ መጨረሻና የኢትዮጵያ እጣ ፋንታ የተነገሩ ትንቢቶች

ዲያቆን ረዳ ውቤ

“ኤርትራም ወደ እናት ሀገሯ ትመለሳለች”
ለአምላክ የቀረቡ ቅዱሳንና ንጹሃን ሰዎች ወደፊት ገና እነሱ ያልኖሩበት ዘመን ሁኔታ አስቀድመው የማወቅ ጸጋ ስለሚሰጣቸው ” እንዲህ ይሆናል: ይሄ ይመጣል ይሄ ይሄዳል ” እያሉ ይናገራሉ :: እነዚህ ቅዱሳን የሚናገሩት እውነት ትንቢት ሲባል እነሱ ተናጋሪዎቹ ደግሞ ነብያት ይባላሉ:: የሚመጣውም ትውልድ አንብቦ ወደፊት ለሚሆነው ነገር ይዘጋጅ ዘንድም የትንቢት መጽሐፍት ይጽፋሉ:: ለምሳሌ በመጽሓፍ ቅዱስ ከትንቢተ ኢሳይያስ ጀምሮ ያሉት የትንቢት መጻሕፍቶች በሙሉ በየግዜው የሚከሰተውን ነገር አስቀድመው የሚናገሩ መጻሕፍት ናቸው::
በሀገራችንም በርካታ ቅዱሳን በሀገርም ላይ ሆነ በግለሰቦች ላይ ስለሚከሰት ጉዳይ : በርካታ ትንቢቶችን ተናግረዋል:: በተለይ በሀገር ዙርያ ትንቢት የተናገሩ ብዙ አባቶችን መጥቀስ ይቻላል:: የወሊሶው አባ ወልደ ትንሳኤ( በኋላ አቡነ ዴዎስቆሮስ) የታወቁ አጥማቂ ነበሩ:: አጋንንቱን እየገዘቱ ያናዝዙት ነበር:: እሳቸውም የሚናገሩት ትንቢት መሬት ወድቆ አያውቅም ነበር::የመቄቱ አባ አዳነ ካሳውም ይሄ ጸጋ የተሰጣቸው ልዩ አባት መሆናቸውን የሚያውቃቸው ያየና እሳቸውን የሚሉትን የሰማ ብቻ ነው::
እኔ በእድሜዬ ባህታዊ ገብረመስቀልን አስታውሳለሁ:: በ1980ዎቹ መጀመርያ ” ትልቁ ዘንዶ አራት ኪሎ ላይ ወደቀ:: የሱን ደም የነኩትም በሙሉ እፍረት ገጠማቸው” እያሉ ይናገሩ ነበር:: ያኔ ልጅ ብሆንም በደንብ እሰማቸውም አስታውስም ነበር:: ሲፈቱትም ዘንዶው አስተዳደሩ ወይም መንግስቱ እንደሆነ ደሙን የነኩትም የኢሰፓ አባላት እንደሆኑ ሲያስተምሩ በጆሮዬ ሰምቻለሁ::ያሉት አልቀረም:: ጥቂት አመታት ቆይቶ የኮሎኔል መንግስቱ አስተዳደር ወደቀ:: ኢሰፓም ፈረሰ::ባህታዊ ገበረ መስቀል አሁን ያሉበት ሁኔታ ለብዙዎች ያልተዋጠ ቢሆንም በግዜው ግን ብዙ የተናገሯቸው ትንቢቶች ደርሰዋል::
አሁንም ስለዚህ መንግስትና ስለመጻኢ ያገሪቱ ሁኔታ በርካታ አባቶች በማሳሰቢያ ጭምር ትንቢት እየተናገሩ ነው:: ይህንንም ለመስማት ወደ ትላልቆቹ ያገራችን ገዳማት በንግስ ግዜ ብቅ ማለት በቂ ነው:–ግሸን : ላሊበላ : ዝቋላ : አክሱም እና ሌሎችም ገዳማት ያሉ መነኮሳትና ባህታውያን ሰንሰለት ታጥቀው ማይክራፎን ይዘው በየግዜው ይናገራሉ:: አጭበርባሪው በበዛበት በዚህ ክፉ ዘመን ባህታዊ ሁሉ ይታመናል ባይባልም : በተለያየ አጋጣሚ ከታመኑ አባቶች ሲነገር የሰማሁትንና ዘግቤ የያዝኩትን ላካፍላችሁ::
በመጀመርያ ስለ ሀገራችን ኢትዮጵያ::
በሀገራችን በኢትዮጵያ በቅርብ ግዜ ይሆናል ተብሎ ከሚነገረው ትንቢት አንዱ እንዲህ ይላል::
“በኢትዮጵያ አህዛብ ጦርነት ይጭራሉ:: በኢትዮጵያም ላይ እሳት ይነዳል::እሳቱም ጉዳት ያደርሳል :: የፈጣሪውን ስም የጠራ ግን ይድናል::ጸልዩ”
ማን እና ምን ማለት ይሆን?
Ethiopia_(1)
እንደገባኝ ከሆነ ኢትዮጵያ ላይ ጦርነት የሚያውጁ ሀገራት ይኖራሉ ብዬ ገምታለሁ:: እንዳለመታደል ሆኖ ጎረቤቶቻችን ባብዛኛው የሚፈልጉን ለጠብ ነው:: ሱማሌ ኢትዮጵያ ጦር ለመስበቅ የምትፈልገው አጋጣሚ ነው:: ከጥንት ጀምራ ኢትዮጵያ ላይ እሳት ያላነደደችበት ግዜ የለም:: በአጼ ሃይለሥላሴ ግዜ: በዘመነ መንግስቱ ሁለት ግዜ ጦርነት ከፍታብናለች:: ሱዳንም የምትታመን ሀገር አይደለችም:: ከኤርትራ ጋር ያለውም የድንበር ጉዳይ እልባት ያገኘ አይደለም:: ከዛ ጋር ተያይዞ አቶ ኢሳይያስም ወዳጅ እንዳልሆኑ ይታወቃል:: ግብጽም ያዙኝ ልቀቁኝ እያለች ነው::ሌሎችም በቅርብ ርቀት ያሉ አረቦች የጥላቻቸው መጠን ልክ የለውም:: የስንት ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን ሬሳ እደላኩልን ሁላችን የምናውቀው ነው:: ምናልባት ከነሱ አንዱ ይሆን ጦርነት የሚያነሳብን ወይስ ሌላ.? ማንንም ሀገር የማጥላላት ዓላማ የለኝም:: ግን ከሁነኛ አባቶች የሚነገሩ ትንቢቶች ስህተት ናቸው ብዬ ስለማላስብ ሀገሬ ለከፉ ቀን ትዘጋጅ እላለሁ::
ትንቢት ስለ ወያኔ
በርካታ ባህታውያንና መነኮሳት ስለ ገዥው አካል የሚናገሩት ነገር አንድ ነው:: እሱም እንዲህ ይላል
“ይሄ መንግስትም( ወያኔ) እንደ አመድ ቡን ብሎ ይጠፋል:: ብዙዎቹም ሀብታቸውን እንኳን የትም ይዘው ለመሄድ እድሉን አያገኙም:: “ምነው” የሚሉበት ግዜም ይመጣል:: ኤርትራውያንም ኢትዮጵያ ውስጥ እህል ውሃ አላቸው::
እንደ አመድ ቡን ብሎ መጥፋት ምን ማለት እንደሆነ ለመረዳት ተቸግሬያለሁ:: አመድ ቦኖ ሲጠፋ የት እንደገባ እንኳን አይታወቅም:: ብን ብሎ ይጠፋል::ምናልባት እንደዛ ማለት ይሆንን? ፈጣሪ ይወቀው:: ግፍ የሰሩ ሰዎችም ፍርድ ፊት መቅረባቸው የማይቀር ይመስላል:: “ምነው” ብለው እስኪጸጸቱ ድረስ ፍርዳቸውን ይቀበላሉ::
አስከፊው ግን ከወያኔ በኋላ ስለሚኖረው ሁኔታ የሚነገረው ነው::
ትንቢት ከወያኔ ውድቀት በኋላ
በዚያን ግዜ የአህዛብ ንጉስ ይነግሳል:: ለቤተ ክርስትያንና ለክርስትያኖችም መልካም ያልሆነ ግዜ ይሆናል:: ደም ይፈሳል:: ብዙ በዳር ሀገር ያሉ ክርስትያኖች መክራ ያገኛቸዋል:: ሰማዕትነት ይቀበላሉ:: ትልቅ ክብርም ያገኛሉ::ከሰማዕትነት ይቆጠርላቸዋል:: ብዙ ወጣቶችም ይሄን ክብር ይቋደሳሉ:: እንደ ቅዱስ ጊዮርጊስ እንደ ቅዱስ መርቆርዮስ ሰማዕትነት ይቆጠርላቸዋል:: የኑሮ ውድነቱም የከፋ ይሆናል:: የኤድስ በሽታም የሚመሰገንበት ግዜ ይመጣል:: በኢትዮጵያም የሚቆመው መንግስትለ ዓለም መንግስታትም ያስቸገረ ይሆናል:: ነገር ግን ስለ ቅዱሳን ጸሎትና ምልጃ እድሜው አጭር ይሆናል”
ይሄም ምን ማለት እንደሆነ ትክክለኛውን ትርጓሜ እንዲህ ነው ማለት ባልችልም ምናልናትም እምነቱ የተለየ ሰው በኢትዮጵያ ላይ ይሾማል:: ኤድስ ለንስሓ ግዜ የሚሰጥ በሽታ ነው:: ምናልባትም ለንስሓ ግዜ የማይሰጥ አጣድፎ የሚገድል በሽታ ሳይሆን አይቀርም::
ትንቢት ስለ ንጉሥ ቴዎድሮስ
” ኢትዮጵያን በዘንግ አርባ አመት የሚገዛ ንጉሥ( ቴዎድሮስ ይሉታል) ይነግሳል:: የሚነሳውም ከምስራቅ ነው:: በሱ ዘመን ስደት ወደ ኢትዮጵያ ይሆናል:: አንድ እንጀራ ለአስር ሰው ያጠግባል:: በሱ ዘመን እንኳን የሰው የንጨት ጠማማ አይኖርም:: ኤርትራም ወደ እናት ሀገሯ ትመለሳለች:: ፍቅርና አንድነት ይሆናል:; የተከፈለው ሲኖዶስም አንድ የሚሆነው በሱ ዘመን ነው::ኢትዮጵያ እጅግ ታላቅ ሀገር ትሆናለች::በሱ ዘመን የሚነሱትም ፓትርያርክ እጅግ የበቁና ገቢረ ተአምር የሚያደርጉ ይሆናሉ:: “
ethiopia map
ትንቢቱን ከተናገሩት አባቶች ደጋግሜ ማብራርያ የጠየኩት ይሄንን ክፍል ነው:: ማብራርያውም ይሄን ይመስላል:: ዘንግ የተባለው ያለ ጦርነት በፍቅር በሰላም ማለት ነው::በዚህ ሰው ንግሥና ዘመን በኢትዮጵያ ፍጹም ሰላም ይሆናል:: በሀሪቱም በረከት ይዘንባል:: ከሌላው ሀገር ተለይታም የጥጋብና የበረከት ሀገር ትሆናለች:: የበርካታ ሀገር ስደትኞችንም የምታስተናግድ የስደተኞች መጠለያና ማረፍያ ትሆናለች:: ለዘመናት ደም ሲቃቡ የነበሩት ኤርትራና ኢትዮጵያም አንድ ይሆናሉ:: ሁለቱ ወንድማማች ህዝቦች ወንድማማችነታቸውን አድሰው በሰላም በፍቅር ይኖራሉ:: የተከፈለው ሲኖዶስም አንድ የሚሆነው በሱ ዘመን ነው:: በዛ ዘመን የሚሾሙትም ፓትርያርክ ሕዝብን ከአምላኩ የሚያስታርቁ : ሀገርን በጸሎት የሚጠብቁ : ተአምር የማድረግ ጸጋ የተሰጣቸው ትልቅ አባት ናቸው::
ቴዎድሮስ ማነው? የሚነግሰውስ መቼ ነው?
ሌላው ብዙ የጠየኩትና የተመራመርኩት ነገር ቢኖር ስለ ቴዎድሮስ ማንነት ነው::
በዚህ ዙርያ ሁለት ነገሮችን ሰምቻለሁ:: አንዱ ቴዎድሮስ ማለት የተሰወረው ነአኩቶለአብ ነው እሱ ነው ተመልሶ መጥቶ ኢትዮጵያን የሚመራው የሚል ነው:: ይሄንን የሚሉት አንድ ሰው ብቻ ናቸው የገጠሙኝ:: ትልቅና የተከበሩ የሃይማኖት አባት ስለሆኑ የሳቸውንም ማብራርያ ጻፍኩት::

ብዙዎቹ ግን የሚሉት ቴዎድሮስ ሌላ ነው እሱም ተወልዷል :: አድጓል:: መሉ ሰው ነው:: መሰረቱም ከቀድሞዎቹ ነገስታት ወገን ነው:: የሚቀባው አባት ብቻ ነው የቀረው የሚል ነው:: ብዙዎቹ እንደሚሉት ከሆነም ቴዎድሮስ ባሁኑ ሰአት ወደተለያዩ ቅዱሳት ገዳማት በመጓዝ ከአባቶች በረከት እየተቀበለ እንደሆነ ተነግሮለታል:: በእምነቱ ጻድቅና ለማንም የማያዳላ: ለድሃና ለተበደለ የሚፈርድ እውነተኛ ዳኛ እንደሚሆንም ይነገራል::
ነገር ግን አሁን በየቦታ ” ቴዎድሮስ ማለት እኔ ነኝ ” እያሉ በየቦታው እንደሚለፈልፉት እንዳይደለና እንደዚህ የሚሉት ብዙዎቹ በሀሰት መናፍስት እየተመሩ የሚያብዱ መሆናቸውን ብዙ አባቶች ያስጠነቅቃሉ::
ሲጠቃለል
ወያኔ መውደቁ አይቀርም:: አወዳደቁ ግን እጅግ የከፋ እንደሚሆንና እንደአመድ ብን ብሎ እንደሚጠፋ::
በኢትዮጵያም ላይ የአህዛብ ጦርነት እንደሚነሳ:: ያም ብዙሰዎችን እንደሚለበልብ :: በዚያን ዘመንም እምነቱ ልዩ የሆነ ሰው መሪ እንደሚሆን: በሱም ዘመን ኑሮ ውድነቱ የከፋ እንደሆነ: በተለይ ለቤተ ክርስትያና ክርስትያኖች የመከራ ግዜ እንደሚሆን ነገር ግን ግዜው አጭር አንደሆነ::በመጨረሻ ግን ኢትዮጵያን በዘንግ የሚገዛ ጻድቅ መሪ እንደሚያስተዳድራት የ ኤርትራና የኢትዮጵያ ችግርም እንደሚፈታ ተነግሯል::ቤተክርስትያንም ከአስመሳዮች የምትላቀቅበት ወቅት እንደሚሆንና የሁለቱም ሲኖዶስ ፍጹም እርቅ የሚፈጸመው በዚያን ግዜ እንደሚሆን ተነግሯል::ቴዎድሮስ የማንንም እርዳታ የማይሻ : ራሱ እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ለመታደግ በራሱ ሃይል: የሚልከው ስለሆነ “ቴዎድሮስ ይሄ ነው ያ ነው: በዚህ መጣ በዚህ ሄደ” በሚል አጓጉል ሀሰት ምእመናኑ እንዳይወናበድ ያስገነዝባሉ::
ክፉውም የሚርቀው መልካሙም የሚቀርበው በጸሎት ነውና የሁሉም ገዳማውያን ተመሳሳይ መልዕክት አንድ ነው ” የመከራ ዘመን ከፊታችን አለና ተግታችሁ ጸልዩ:: እግዚአብሔር ያርቀው ዘንድ”

በመጨረሻ
ይሄን ጽሁፍ የሚያነብ ሰው ከሁለት ጎራ ሊመድበኝ እንደሚችል ከወዲሁ ይታየኛል:: የመንግስት ደጋፊ የሆነ ሁሉ በመንግስታችን ላይ የሚያሟርት ቀልደኛ ፌዝ ብሎ ሊዘብትብኝ እንደሚችል እገምታለሁ:: የፈጠራ ድርሰትም የደረስኩ የሚመስለው ሊኖር ይችላል:: እኔ ግን የሰማሁትን ነው የነገርኳችሁ:: አለማመን መብታችሁ ነው:: ግን በልባችሁ አስቀምጡት:: ከሁሉም በላይ ስለሀገራችን ስለሕዝባችን አንዲት ደቂቃም ብትሆን በየቀኑ እንጸልይ::
አበቃሁ::

No comments: