✍ ዘርአዳዊት ዘ-ኢትዮጵያ
ዛሬ መጋቢት ፳፫ ቀን፣ ፳፻፲፭ ዓመተ ምሕረት የአባታችን ሊቀ ሊቃውንት አለቃ አያሌው ታምሩ ፻ኛ ዓመት የልደት ቀን መታሰብያ ነው። አለቃ የማውቃቸው ስለ 'ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን' ሳጠናና የነበሩኝ ጥያቄዎች መልስ ለማግኝት በምጥርበት ወቅት ነው። በዚህ ምክንያት የዮቲዮብ (YouTube) ድረ ገጽ ሳስስ አለቃ አያሌው ታምሩ ከአሜሪካ ድምጽ ራድዮ (VOA) በ፬ ክፍል ያደረጉት ቃለመጠይቅ አግኝቼ በማድመጤ በጭንቅላቴ ሲመላለሱ የነበሩ ጥያቄዎች መልስ ያገኝሁበት ነበር። በተለይ በፖትርያርክ አቡነ ጳውሎስ የነበረኝ ጥያቄ ተገቢ መልስ በማግኝቴ አዕምሮየ ሠላም አግኝቷል።
አለቃ ለእግዚአብሔር እውነት ብቻ የቆሙ እንጂ ለሥጋዊ ሓሳብና ፍላጎት ቦታ የሌላቸው የፅናት ተምሳሌት ናቸው። ከአለቃም ይህንን በማየትና በመስማት መማር ይቻላል። በተለይ ለኢትዮጵያና ኢትዮያዊነት መጠበቅ ያላቸው ትጋት የአሁኑ ትውልድ ሊማርበት ይገባል። አለቃን ሳስብ ተስፋ ፣ እውነትና የአሸናፊነት መንፈስ ይወረኛል እፅናናለሁ። ምክንያትም ሁሉም በጊዚያዊ ነገር ተሸንፎ ከእውነት በራቀበት ወቅት እውነትን ይዞው ብቻቸውን የቆሙ አባት ነበሩና።
No comments:
Post a Comment