EAR

አዲስ ነገር

Friday, 22 January 2016

ይቺ ፍልስፍና ምንድር ነች?

      ዘርአዳዊት -ኢትዮጵያ


    ፍልስፍና ፈጣሪ የለም ብሎ ማመን ነች? አይደለችም ።የራስን እምነት ትቶ የሌላ ማጥላላትና ማሾፍ ነች? አይደለችም። ታድያ ምንድር ነች? የፍልስፍና ጀማሪዎች የሚባሉት ግሪኮች ፍልስፍና የጥበብ ፍቅር ነች በማለት ይገልጽዋታል።መጽሓፍ ቅዱስም የጥበብ መጀመርያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው ይላል።ታድያ የፍልስፍናን ትርጉም በማዛባት  ፈላስፎች ነን የሚሉ ጥቂት ሰዎች እግዚአብሔር የለም ብለው በማመናቸው(ይህ የሚሉት ለሌላ ሰው ቢሆንም ልቦናቸው የሚሰጣቸው መልስ ግን ራሳቸው ያውቁታል) የሌላን ሰው እምነት ማብጠልጠል  የፍልስፍና መገለጫ ስያደርጉት እዚሁ ፌዝቡክ ላይ እያነበብን ነው።እነዚህ ሰዎች ያልገባቸው ነገር ፈጣሪ የለም ብሎ ማመን ራሱ እምነት መሆኑ ነው።ይህም የሚያረጋግጥልን የሰው ልጅ ፍጡር በመሆኑ ያለ እምነት ሊኖር እንደማይችል ነው።የሰው ልጅ ነጻ ፍጡር እንደመሆኑ በተሰጠው ነጻነት ልክ የፈለገውንና የገባውን ነገር የማመን(freewill) የማይሸራረፍ ፈጣሪ የሰጠው መብቱ ነው።ይህ መብት ግን ፍልስፍና ባልገባቸው ሰዎች የክህደትና የማጥፍያ መሳርያ ሆኗል።

   ፍልስፍና የፈጣሪን መኖርና አለመኖር የምታረጋግጥ ሳትሆን ከፈጣሪ ዘንድ የምትፈልቅና የሰውን ልቦና የምታቀና የብርሃን ምንጭ ነች።ይህንን ባለመገንዘብ የሰው ልጅ ፈጣሪ የለም የማለት ሙሉ መብት ቢኖረዉም(ፈጣሪ ከሌለ ማን እንደፈጠረው መልስ የመስጠት ግዴታ አለበት) ፍልስፍና ግን ህልወተ እግዚአብሔር አትክድም።ፋላስፋ ነኝ ባይ ካልካደ በስተቅር።ፍልስፍናና ፋላስፋ ነኝ ባይ ለያይቶ ማየት ተገቢ ነው።አማኝ እና -አማኝ የሚሉት ቃላት የሚያስረዱንም አማኝ የሚለው ቃል መነሻ መሆኑ ነው።ማለትም -አማኝ እምነቱ የሚጀምረው አማኝን በመቃወም ነው።ይህም የምትለዋን አፍራሽ  ቅድመ ቅጥያ  በመጨመር ነው።ይህም የሚያስገነዝበን -አማኝነት መነሻው አማኝነት ነው ማለት ነው።ኢ-አማኝ አማኝ ላይ ጥገኛ እንጂ ብቻውን ሊቆም የማይችል ነው።ኢትዮጵያዊው ፋላስፋ ዘርዓያቆብ እንዲህ ይላል።‹‹ነፍሴ በእግዚአብሔር ዘንድ የተከበረች ትሁን ጆሮዎችም ሰምተው ይደሰቱ።እኔ እግዚአብሔርን ፈለኩት መለሰልኝ።አሁንም እናንተ ወደ እርሱ ቅረቡ ያበራላችሁማል ፊታችሁንም አያሳፍርም።እግዚአብሔርን ከኔ ጋር ከፍ ከፍ አድርጉት አብረን ስሙን እናንሳ።››