EAR

አዲስ ነገር

Monday, 13 November 2017

“አስማተኛ ወይም ጠንቋይ አይደለሁም” የታገዱት መምህር ግርማ ወንድሙ።



©ላይፍ መጽሄት
ላይፍ፦ በቤተክርስቲያን ውስጥ ተገኝተው፡የጥምቀትናየትምሕርት አገልግሎት እንዳይሰጡ የታገዱበት ምክንያት ምንድነው? መምህር ግርማ፦ ምክንያቱም፡ ሰው በመዳኑና የዲያቢሎስ ምሥጢር በመጋለጡ፥ እንዲሁም ሕብረተሰቡ ስለክፉው መንፈስ፡ ግንዛቤው እየጨመረ መምጣቱ ነው።
ላይፍ፦ ለስንት ዓመት አገልግሎት ሰጥተዋል?
መምህር ግርማ፦ 1993 . ጀምሮ እዚህ አዲስ አበባ ያልተቋረጠ አገልግሎት ሰጥቻለሁ።
ላይፍ፦ ለምን ያህል ህሙማን ከህመማቸው የመፈወስ እና ትምህርት አገልግሎት ሰጥተዋል?
መምህር ግርማ፦ 4 ሚሊየን ሰው የፈውስ አገልግሎት ሰጥቻለሁ፡፡
ላይፍ፦ በተለይ በምን አይነት ህመም ሲሰቃዩ የነበሩ ሰዎችን አድነዋል?
መምህር ግርማ፦ ዓይናቸው የጠፋ፥ ሰውነታቸው አልታዘዝ ብሎ አልጋ ላይ ውለው የነበሩ፥ እጅና እግራቸው ሽባ የነበሩ ሰዎችን ፈውሻለሁ።
ላይፍ፦ ሁላችሁም የእግዚአብሔርን ቃል፥ የእመቤታችንን በረከት የምታስተምሩበት ቤተክርስቲያን ለምን እንዲህ አይነት መከፋፈል መጣ ብለው ያስባሉ?
መምህር ግርማ፦ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ፡ እንክርዳድ በስንዴው መሐል እንደሚዘራው ሁሉ፡ ያም በቤተክርስቲያን ውስጥ አለ። ገበሬው፡ "መልካም ስንዴን ዘራ" የሚለው ከውጭ አይደለም፤ ዘሩ እዚያው ቤተክርስቲያን ውስጥ ነው። ስለዚህ በቤተክርስቲያን መንፈሳዊ ሕይወትና በልቦና ውስጥ መጀመርና በሥጋ ሕይወት መጀመር ልዩነት አለው። አምኖ መጀመርና ሳያምኑ መጀመር የእዚያን ያህል ነው። ሰሞኑን ወደ ቤተክርስቲያን ገብተው የሚኖሩ በጣም ብዙ ናቸው። እነዚህ ከተለያዩ የአስማት ሥራ ጋር ወደ ቤተክርስቲያን ሲጠጉ፡ ብዙ መልካም ነገር አይጠበቅባቸውምና፡ ይህንን በሚመለከት ‹‹በማለዳ መያዝ›› የሚለው መጽሓፌ ላይ ሰፋ ባለ መልኩ አስቀምጬዋለሁ። ንጹሕ የአምልኮት ፍላጎትና እንዲሁ ደግሞ በደብዛዛው በሚመላለሱ ሰዎች መካከል ዲያቢሎስ በደንብ ይሠራል። በተለይ ኦርቶዶክስ እምነት ላይ፡ ሰይጣን ከፍተኛ ትኩረት ይሰጣል። ከታሪክ እውነታም አንጻር እነዚህ ሰዎች ሕይወት ውስጥ የተለየ እድል አለ። ገብቶ ይቀመጥና በጎውን መጥላት፥ መልካሙን እንደክፉ ማየት። ማሳደድ ያለው መናፍቆች ላይ ሳይሆን እኛ ጋር ነው ያለው። ይህ ደግሞ የሃይማኖቱ አንዱ በረከት ነው። ለምን? ፈሪሳውያን ክርስቶስ በመጣ ጊዜ፡ እምነቱን ተራ ወግና ተራ የሆነ የይስሙላ አድርገውት ነበር። ሂደት ደግሞ እንደዚሁ በቆየን ቁጥር፡ የአዲስ ኪዳንንም ሕይወት እንደዚያ ነው የሚሆነው። ወደ ፈሪሳውያን ጠላት ይሄዳል፡ በዚህ ጊዜ እውነቱ እየጠፋ በቤተክርስቲያን ውስጥ ጣልቃ ይገባሉና ያንን ለመለየት የመንፈስ ቅዱስ ሥራም፥ የአጋንንት የቅንነትም ሥራ ስለሚያስፈልግ፡ ዛሬያ ቅንነቱና በጎነቱ፡ በክፋት፥ በተንኮል፥ በምቀኝነት የተሞላ ስለሆነ ሂደት አንድ ሊያደርገን አልቻለም።
ላይፍ፦ ብዙ ሰባኪያን ወደ እርስዎ ፕሮግራም የማይመጡት ለምንድነው?
መምህር ግርማ፦ ይህንን የፈውስ ሂደት ስላልለመዱት፡ ልክ እንደ መተት፥ እንደ ጠንቋይ አሰራር አድርገው እስከዛሬ ድረስ ሲያወሩ እንደቆዩ፡ ያው የተለመደ ነገር ነው። ስላልተለመደ እንግዳ ነገር ነው የሆነው። በተለይ በግለሰብ ጸጋ አልተለመደም። ይህንን ያልተለመደ ነገር እንዲህ ሲወጣ ሁሉም እየተረባረበ ማጨለም ነው የሚፈልገው። የእግዚአብሔር ሥራ ደግሞ ስለማይጨልም ሂደቱን ጠብቆ ይበራል። ከዚህም በፊትም የተደረጉብኝ ዘመቻዎች ብዙ ናቸው፡ ይህ ብቻ አይደለም። ይህ እንዲያውም የመጨረሻው ደካማ ነው። የቤተክርስቲያን ሰዎች መንፈሳዊ አንድነታቸው በክፉ ሰዎች መንፈስ ተመቷል። በራስ እይታም ተመቷል። የምቀኝነት መንፈስ አጠናክረው በመያዛቸው ምክንያት፡ የእግዚአብሔር ጸጋ በረከት መለያ መንፈስ አጥተዋል። አንድነትና ተስማምቶ መዝለቅን በዚህ ዘመን ውስጥ የምንጠብቀው ጉዳይ አይደለም። ግን እውነት ዞሮ ዞሮ ደረጃዋን ጠብቃ ስለምትወጣ፡ ያን ያህል አስጊ አይደለም ማለቴ ነው።
ላይፍ፦ እርስዎ አለኝ የሚሉት የፈውስ ጸጋ ከየት የመጣ ነው ይላሉ?
መምህር ግርማ፦ ይህ እኮ፡ አንድና አንድ ሲደመር፡ ኹለት ነው፡ እንደሚባለው ዓይነት ፎርሙላ፡ ወጥ አድርገህ የምታሳየው ነገር አይደለም። ይህ፡ በጸሎት፥ በስግደት፥ በቅዱስ ቁርባን፥ በመመጽወት፡ ከሰማይ የሚለቀቅ እንጂ፡ ከማንኛውም ሰው የምትገዛው ወይም የምትለውጠው ትርፍ ያለው ነገር አይደለም። ይህ ከሰማይ የሚሰጥ ፀጋ እንጂ፡ በሥጋዊ ጥበብ፥ ዘዴ፥ ወይም ምርምር ወደ ላብራቶሪ የሚመጣና የሚገኝ አይደለም። ምክንያቱም የእግዚአብሔር አሠራር ነው። የእግዚአብሔር አሠራር ደግሞ፡ ዓለምም ኾነ ሥጋውያን አያውቁትም። መንፈሳውያንም ተቸግረዋል፡፡ በዚህ ዘመን ያሉ የገዛ አባቶቼ እንኳን ሳይቀሩ፡ ይህንን መንፈሳዊ ጸጋ ለመቀበል በጣም ይቸገራሉ። ምክንያቱም፡ "ከእኛ በኩል ካልፈሰሰ?" ነው እኮ አሁን ችግሩ። "ከእኔ በኩል ካልፈሰሰ? እንዴት በዚህ ዘመን፡ ከእግዚአብሔር ይመጣል?" የሚል ዋጋ ቢስና ተስፋ አስቆራጭ የመንፈሳዊ ሕይወት ጉዞን የለመዱት ባሕሪለማንጸባረቅ ሲሞክሩ ነው፡ አሁን ነገሮች ወደዚህ አይነት አጣብቂኝ ውስጥ የሚገቡት።
ላይፍ፦ እርስዎ ተሰጥቶኛል የሚሉት የመንፈስ ጸጋ ስያሜ ሰጥተውታል?
መምህር ግርማ፦ እንደዚህ ያለ ነገር የለም እንጂ፡ ምን ስም ይሰጠዋል? "ክፉ መናፍስትን የሚቃወም የእግዚአብሔር መንፈስ!" ነው።የእግዚአብሔር መንፈስና ክፉ መንፈስ ደግሞ አይገናኙም። የእግዚአብሔር መንፈስ የእግዚአብሔር ስጦታ ነው። የእግዚአብሔር ስጦታ ደግሞ ክፉውን መለየት፤ ክፉውን ማስወገድ ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ፡ "አጋንንትን አወጡ" ይል የለም እንዴ? በአሁኑ ዘመን፡"አጋንንት አስገባ" ቢባል ሁሉም ይወደኛል። አጋንንት ማስወጣት እኮ ነው የተለየ ጠንቋይ ያደረገኝ።
ላይፍ፦ አለኝ የሚሉት የመንፈስ ጸጋ ወደ ሌላ ሰው ማስተላለፍ ይችላሉ? ወይስ እርስዎ ጋር ነው ሊቀር የሚችለው? መምህር ግርማ፦ የኤልያስ መንፈስ፡ በኤልሳዕ እንዳደረ ሁሉ፡ የፈለገው ሁሉ ያገኛል። እኔም የማስተምረው እኮ፡ ክርስቲያኑ ራሱን ችሎ እንዲቆም ነው፤ ጠላቱን እንዲጋፈጥ፤ ክፉ መንፈስ እንዲያሸንፍ፤ የዲያቢሎስ ትውልድ መሆኑ እንዲቆም፤ ከዚያም በላይ የመንፈስ ቅዱስ ሥራ የእግዚአብሔር ክብርና ኃይል እየጨመረ እንዲመጣ፤ የዓለም ጥበብ ከእግዚአብሔር መላዕክት አሠራር ጋር ክርስቲያኖች በረከት ውስጥ እንዲገቡ ነው። አሁን ለምሳሌ በአሜሪካ በስልክ የሚሸኝላቸው ብዙ ሰዎች አሉ። በእጄ ማስረጃ አለኝ። በስልክ የሚሸኝላቸው ራዲዮ አቢሲኒያ ላይ ከቁጥር 1 ጀምሮ እስከ 34 ድረስ ያለውን ትምህርት በመከታተል እየጸለዩ፥ እየሰገዱ፥በመቁጠሪያ እየቀጠቀጡ፡ መንፈሱን ያዳክሙታል። ከዚያ በኋላ መንፈሱ ራሱ፦ "እኔ ዓይነጥላ ነኝ" "ቡዳ ነኝ" "አብሬ ነው የተወለድኩት" እያለ ይነግራቸዋል። በመጨረሻ ከተዳከመ በኋላ፡ አንዳንዴ ራሱ፦ "ሸኙኝ" ብሎ ይደውላል። በእጄ የቀረጽኳቸው 200 በላይ በስልክ የሸኘሁላቸው ሰዎች አሉ። አሁን አባቶች ይህን ነገር ሲሰሙ ይደነግጣሉ። ምክንያቱም፡ "እንዴት በስልክ ሰይጣን ይወጣል?" ብለው አንድ ወቅት ላይ አቅርበው ጠይቀውኛል።ስለዚህ ጸጋው የቤተክርስቲያን እንጂ የእኔ አይደለም።መቁጠሪያው የቤተክርስቲያን ነው፤ ውዳሴው የቤተክርስቲያን ነው፤ መላከ ትግሉ የቤተክርስቲያን ነው። ከዚህ ውጪ እኔ የያዝኳቸው የምትሀት አሰራር የለም። ስለዚህም ሁሉም ህዝብ በውጭ ዓለም ያለው፡ በተለይ ከክፉ መንፈስ ጋር ያለውን ፍልሚያ በሚገባ ስለተገነዘበ፡ እያንዳንዱ ራሱ በመቁጠሪያ እየተጠቀመ የሸኘውም አለ።
ላይፍ፦ አባቶች እርስዎ የሚሰጡበት መንፈሳዊ ጉባኤ ተገኝተው በረከት ይሰጡ ነበር ወይ?
መምህር ግርማ፦ እኔ በማገለግለው ላለመገኘት ብዙዎችይሸሻሉ፤ ተሰልፈው፥ ዝቅ ብለው፡ የሕዝብን ችግር ለማየት እስከ አሁን በጎ ህሊና አላገኘሁም።
ላይፍ፦ አባቶች፡ እርስዎ በሚሰጡት መንፈሳዊ አገልግሎት አስተያየታቸው ምንድነው?
መምህር ግርማ፦ ብዙዎች ይህንን መንፈሳዊ ድርሻ ለመወጣት በማደርጋቸው ጥረቶች ላይ በጎ ድጋፍ የላቸውም። ከተለያዩ አይነት መንገድ ለመዳንም ይመጣሉ። ነገር ግንአንዳንዶች እንዲያውም፡ "የሸናሻም መተት ይህን ያደርጋል" "የሸናሻም አስማት ይህንን ይሰራል" እያሉ፡ለሐሰት አሠራር ትልቅ ድጋፍና፡ ለሰይጣን አሠራር ትልቅ ሞራል ሲሰጡ ነው የሚሰማው።
ላይፍ፦ ይህንን እርስዎ የሚያደርጉትን መንፈሳዊ አገልግሎት፡ ሌሎች አባቶች ያምኑበታል?
መምህር ግርማ፦ እኔም በጣም ግራ የሚገባኝ፡ ዲያቢሎስ የሚያደርገው ጥቃት በመጽሐፍ ቅዱስ በረጅሙና በስፋት ጥልቀት ባለው ሁኔታ ተገልጿል። ሐዋርያት አጋንንትን እያወጡ የሰዎችን ደህንነት ሲያበለጽጉ ይታያል። በቤተክርስቲያንም እንደዚሁ በመንፈሳዊ አገልግሎት በመንፈስ ቅዱስ ሥራ እንደሚሠራ ይታወቃል። እንግዲህ ሰዎች በክፉ መንፈስ አሠራር ወይም አያምኑም፡ አልያም በእግዚአብሔር አሠራር አያምኑም። በዚህ መንታ መንገድ ላይ መታየት አሁን አይቻልም። ምክንያቱም የእግዚአብሔር ሕዝብ በዲያቢሎስ ተጠቅቷል። ወይ ዲያቢሎስ እንዲበላ ማድረግ ነው፤ አልያም በቤተክርስቲያን መንፈስና ጸጋ ህዝቡ ችግር ውስጥ ገብቶ ችግሩን ማየት ነው። ገለልተኛ ሆኖ መኖር አሁን አሁን ጊዜው አይደለም። ስለዚህ ያምናሉ፡ አያምኑም የሚለው ነገር እርሳው፡ እኔን ቢረዱኝ ደስ ባለኝ። በተሰጣቸው ጸጋ ክፉ መንፈስ ነው ካሉ፡ የእኔን መንፈስ ማውጣት መቻል። ሁሉም ቢተባበሩኝ መልእክት አስተላልፋለሁ። እንዲያውም በቤተክርስቲያን ይኖር የነበረ አስማተኛ መንፈሱን አስወጣንለት ብለው ለዓለም ዜና ቢያቀርቡ ደስ ባለኝ ነበር።
ላይፍ፦ ቤተክርስቲያኗ፡ "ወታደርና ነጋዴ የቤተክርስቲያን አገልጋይ አይሆንም" የሚል ሕገ ደንብ አላት። እርስዎ ግን መንፈሳዊ ሕይወት ውስጥ ከመግባትዎ በፊት ወታደር እንደነበሩና እስጢፋኖስ ቤተክርስቲያን አገልግሎት መስጠት ከጀመሩ በኋላ 1.5 ሚሊየን የሚገመት ቤት ገዝተው እየኖሩ ነው ይባላል፡ በዚህ ላይ ምን ይላሉ?
መምህር ግርማ፦ ዛሬ፡ "ሰማዕቱ" "ሀገር ጠባቂ"የምንለው፡ ቅዱስ ጊዮርጊስም፡ የመቶ አለቃ ወታደር ነበር። ግብጽ ውስጥ ያሉ ብዙ ታላላቅ አባቶችም እንደዚያው ናቸው። በአሁንም ዘመን ያሉ ብዙ መነኮሳቱ እስከ ጳጳሳቱ ድረስ፡ ወታደር የነበሩ ናቸው። ወታደር ማለት የእግዚአብሔርን ስራ አይሰራም ማለት አይደለም። እኔ ደግሞ፡ "ልቀድስ" "ላቁርብ" አላላኩም፤ በተሰጠኝ ጸጋ ላገልግል ነው ያልኩት። ቤት ምናምን የሚሉት፡ ቤቱን የገዛልኝ የተፈወሰ ሰው ነው። ቤቱን የገዛልኝ እግዚአብሔር በሰው በኩል ነው። ቤቱን የገዙልኝ ሰው በተጨባጭ ከጎኔ አሉ። ይህንን እንደ አንድ እንደ ትልቅ ነገር ማንሳት በራሱ ምንን ያመለክታል? ምቀኝነትን ነው፤ ያው ከደማችን ውስጥ የተለመደ ምቀኝነት ስላለ እንጂ፡ እነዚህ ሁኔታዎች በሙሉ እንዳልሰራ የሚያደርጉ አይደሉም።
ላይፍ፦ እርስዎን፡ "አስማተኛ እና ጠንቋይ ናቸው" ለሚሉዎት ሰዎች ምላሽ ምንድነው?
መምህር ግርማ፦ እኔ አስማተኛ ከሆንኩ፡ እኔ ጋር መጥተው አስማቱን ማውጣት ነው፤ እኔ ጋር መጥተው አስማቴ የት ጋር እንደተቀበረ ፈልገው ማውጣት ነው፤ ክንዴ ላይ፥ ወይም እግሬ ላይ፥ ወይም ጭንቅላቴ ላይ እንዳለ፡ ደንበኛ ራጅ ይዘው መጥተው ፈልገው ማውጣት ነው። ወይም መንፈስ ከሆነ ያስወጡልኝ። ቢረዱኝ እኮ ለእኔም ደስ ይለኛል፡ ግልግል ነበር። እስቲ አስማቴን እና አስወጡልኝ እባካችሁ? ስለ እግዚአብሔር ስለ ቅድስት ድንግል ማርያም ብዬ እለምናችኋለሁ።

No comments: