EAR

አዲስ ነገር

Thursday, 4 December 2025

"እኅተ ማርያም" የቅድስት ሀገራችን ኢትዮጵያ ስያሜ በ "አቢሲንያ" ለመተካት ፈልጋ ይሆን?

✍ ዘርአዳዊት ዘ-ኢትዮጵያ 

የእኅተ ማርያም ተከታዮች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሚኅበራዊ ትስስር ድረ ገፆች ኢትዮጵያ የሚለው የቅድስት ሀገራችን ስም "አቢሲንያ" በሚል ተክተው በተደጋጋሚ ማለትም ዘመቻ በሚመስል መልኩ እየተጠቀሙ ነው።

በአክሱም ዘመነ መንግስት ጊዜ ኢትዮጵያ የሚለው ቃል የዛሬዋን ኢትዮጵያ ከጎረቤቶቿ ከእነ ሱዳን ጭምር በመለየት የሚወክላት ስያሜ መሆኑን የአክሱሙ የመጨረሻ ንጉሥ በ976 ዓ.ም ጊዮርጊስ ለተባለው ለኑብያው ንጉሥ በጻፈው ደብዳቤ ላይ "ድልነዓድ ንጉሠ ኢትዮጵያ" ብሏል፤ ይኼ ማስረጃ ስለተገኘለት ነው እንጂ ከዚያ በፊትም መባሉ አይቀርም።

በአክሱም ጊዜም ሆነ እስካሁን ድረስ የእኛ ነገሥታቶቹ ሀገራቸውን የሚጠሩት ኢትዮጵያ የሚለውን ስያሜዋን በመጠቀም ነው። በእርግጥ ከአክሱም ዘመን በፊት የነበረችው ኢትዮጵያ ሱዳንና ኤርትራን ጨምሮ ደቡባዊ የግብጽና የአፍሪካ ቀንድ ግዛትንም የሚያካትት ነበረ። በአክሱም ዘመን የነበረችው ኢትዮጵያ ሱዳንን የምትጨምር እንዳልሆነችና በደቡብ ግዛት መዳረሻዋና ወሰኗ ደግሞ የአዛኒያ መንግስት ጋር እንደ ነበር የተገለጸበት ነገር አለ። የአዛኒያ መንግስት ማዕከሉ የዛሬዋ ታንዛኒያ አካባቢ ነው። 

ኢትዮጵያን ከአክሱም ዘመነ መንግስት በፊት በ25ኛው የግብጽ ሥርወ መንግስት በፒያንኪ ዘመን ካየናት እጅግ ሰፊ ሀገር ነበረች። በአክሱም ዘመነ መንግስት ጊዜ ደግሞ ሱዳንን ቀንሳለች። በእነ ዓጼ ቴዎድሮስና ዓጼ ዮሐንስ ዘመን ደቡብን ክፍል ቀንሳለች፤ በዳግማዊ ዓጼ ምኒልክና ኃይለ ሥላሴ ጊዜ ደግሞ የአሁኑን ቅርጿን ይዛለች። ከደርግ ውድቀት በኋላ ደግሞ ኤርትራንም ቀንሳ ኢትዮጲያ እየተባለች አለች። 

የጥንቷን "ኢትዮጵያ" የሚለውን ስያሜ በመውረስ ከ7500 ዓመታት በላይ እስካሁን እየተጠቀመች የቀጠለችው የአሁኗ "ኢትዮጵያ" ናት፤ ሌላ ሀገር የለም። በዓጼ ዘርዐ ያዕቆብም፣ በዓጼ አምደ ጽዮንም፣ በዓጼ ልብነ ድንግልም ሆነ በዓጼ ቴዎድሮስና በዓጼ ፋሲል አልያም በራስ ቢትወደድ ዓሊ ጊዜ ስማችን ኢትዮጵያ ነበር።  

ቤተ መንግስቱ ከአክሱም ወደ ላስታ ከዚያም ወደ ኃይቅና አካባቢው ከዚያም ወደ ሸዋ ቀጥሎ ወደ ጎንደር ከዚያም እንደገና ወደ ሸዋ ሲዘዋወር የኢትዮጵያ ስም ኢትዮጵያ እንጂ አቢሲኒያ አልነበረም። የነገሥታቱ ማህተም በራሱ "የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግስት" የሚል ነበር። አንድም የኢትዮጲያ ንጉሠ ነገሥት ራሱን "የአብሲኒያ ንጉሠ ነገሥት" ነኝ ብሎ አያውቅም። እንዲያውም ከዳግማዊ ዓጼ ምኒልክ በፊት የነበሩት ነገሥታት "አቢሲኒያ" የሚለውን ቃል ከነመፈጠሩም አያውቁትም።

ሌላው ቀርቶ በ16ኛው ክፍለ ዘመን የመጣው አልቫሬዝ አቢሲኒያ አላለንም፤ እሱ የጠራት "የቄሱ ዮሐንስ" ሀገር በማለት ነበር። ይሁንና ከዚያ በኋላ የመጡ አውሮፓውያን፤  በተለይ ከ18ኛው ክፍለ ዘመን ወዲህ ወደ ሀገራችን የገቡት አቢሲኒያ እያሉ ይጠሩን ነበር። አውሮፓውያን እንደዚያ ቢሉም  የነገሥታቱ ዜና መዋዕሎች ኢትዮጵያ ከማለት በቀር ሌላ ስያሜ አያውቁትም። ይኼ አቢሲኒያ የሚሉት ቃል የእኛ ሳይሆን የፈረንጆች አጠራር ለመሆኑ የሚያስረዳችሁ በፈረንጅ መዛግብት እንጂ በእኛ በኢትዮጵያዊያን አለመኖሩ ሊታወቅ ይገባል።

ይሁንና ኢትዮጵያ በ1920 የሊግኦፍኔሽን መስራችና አባል ስትሆን ፈረንጆቹ የሰጧት ስያሜ የለመዱትን "አቢሲኒያ" ሲሆን፤ ንጉሠ ነገሥቱ ግን ራሳቸውን የሚጠሩት ንጉሠ ነገስት ዘኢትዮጵያ እያሉ ነበር። ለነገሩ የሊግኦፍኔሽኑ ስያሜም ብዙም ሳይቆይ ተቀይሯል። በተለምዶ ብዙ ሰዎች አቢሲኒያ ማለት ሀበሻ ለማለት ነው ይላሉ። ሀበሻ ለማለት ቃሉን ወደ አቢሲኒያ መቀየር ለምን አስፈለገ? ፈረንጆቹ "ሀበሻ" ለማለት ምላሳቸው አይሰራ ይሆን? ወይስ ሆሂያቶቹ በእንግሊዝኛ መዝገበ ቃላት ስለሌሉ ነው? 

ምናልባት ግን Abyssinia የሚለው ቃል Abyss ከሚለው የእንግሊዘኛ ቃል ሳይመጣ አይቀርም😊 ትርጉሙም ገደል ማለት ነው። አቢሲኒያ ማለት ሐበሻ ማለት ነው የሚለውን አባባል ግን በዘልማድ ሳይፈተሹ ዝምብለን ስንቀባበልቸው ከነበሩ ተረት ተረቶች መካከል አንዱ ለመሆኑ ለመረዳት አይከብድም።  ያው ፈረንጆቹ ድሮ በ16ኛው ክፍለ ዘመን ወደ አገራችን በእግራቸው ሲመጡ ብዙ ገደላ ገደል ስላጋጠማቸው Abyss-inia ያሉን ይመስለኛል። አገሬዎቹ ግን እንደዚያ መባላቸውን ያወቁት በ20ኛው ክፍለ ዘመን መግቢያ ላይ ነው።

ለማንኛውም አቢሲኒያ የኢትዮጵያ የጥንት ስም አልነበረም፤ ሆኖም አያውቅም። ይሁንና አውሮፓውያን ባንክ ሲከፍቱልን "ባንክ ኦፍ አቢሲኒያ" አሉት። የኛወቹ ሰወች ደግሞ አቢሲኒያ ሲሉ የሰለጠኑ መስሏቸው ለልጆቻቸው፣ ለባንክ፣ ለንግድ ድርጅት ወዘተ ስያሜ ሲሰጡ ኖረዋል። ነገር ግን ምንም የሚያገናኘው ነገር የለም!! በዚህ በኩል ኩሽ ካልተባልን በዚያኛው በኩል አቢሲኒያ ካላልናችሁ ይሉናል። እኛ ግን የሆነውን እናውቃለን!! የኢትዮጵያ የጥንት ስም አቢሲኒያ ነው የሚል ተረት ተረት አውሪ ካለ ማስረጃውን ወዲህ ይበል!!

ኢትዮጵያ ማለት የቃሉ ትርጉም እነዚያ አዕምሯቸውን የታወሩ ጠላቶቿ እንደሚያወሩት የግሪክ ቃል ማለትም "የተቃጠለ ፊት" ማለት አይደለም።   ኢትዮጵያ ማለት “ለአምላክ የሚሰጥ የወርቅ ሥጦታ” ማለት ነው። ኢት=አምላክ፣ ፈጣሪ፣ እግዚአብሔር ማለት ሲሆን ዮጵ= ቢጫ ወርቅ፣ ውድ ወርቅ፣ ልዩ ወርቅ ማለት ነው። 


No comments: