✍ ዘርአዳዊት ዘ-ኢትዮጵያ | ኢትዮጵያ አውታር
በጽሑፍ የቆየው ጥንታዊ ታሪካችን እንደሚያስተምረን ከኾነ ኢትዮጵያ ወርደ ሰፊ ሀገር ነበረች። ትናንት አፍሪካ ኢትዮጵያ የምትባልበት ዘመን ነበር:: ትናንት የህንድ ውቅያኖስ የኢትዮጵያ ውቅያኖስ የሚባልበት ዘመን ነበር:: ትናንት የአትላንቲክ ውቅያኖስ የኢትዮጵያ ውቅያኖስ የሚባልበት ዘመን ነበር:: ትናንት በአውሮፓ በደቡብ እና ሰሜናዊ አሜሪካ እንዲሁም በሩቅ ምስራቅ ሀገራት ላይ ሥልጣኔን መስርተናል:: በዚህም የተነሳ ዓለም ላይ ኢትዮጵያዊ የዓለም አገዛዝን መስርተን ነበር::
አሁን ሶማሊያ፥ ጂቡቲ፥ ኤርትራ፥ ሱዳን፥ የመን እየተባሉ የሚጠሩት ሀገሮች ሁሉ፡ የኢትዮጵያ አካሎች ነበሩ። ኢትዮጵያዊ አባቶቻችን ይህን ታሪክ በመዝገብ አቆይተውልናል።
አባቶቻችን ይህን ታሪክ እየነገሩን ሳለ፡ ምዕራባውያን ደግሞ፡ እነርሱ በሚፈልጉት መንገድ እንድናስብ ስለሚፈልጉ፡ የረቀቁ ትምህርቶችን የሚነድፉልንን፡ ኢትዮጵያውያንን ወደ ጎን በመግፋት "አባቶቻችሁን አትስሟቸው፤ ውሸታሞች ናቸው" ይሉናል።
እንደዚህ የሚሉን ምዕራባውያንም አሁን ተገንጥለው በሚገኙት በእነዚህ የኢትዮጵያ አካል በነበሩ ቦታዎች የሚገኙትን ሰዎች፡ "ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ናቸው!" ብለን እንድናስብ ይቅርና፡ የምዕራባውያን ተላላኪ ህወሓት ካድሬዎች እንኳን "ኤርትራ" ኢትዮጵያ የነበረች አይምሰላችሁ፡ ይሉናል ።
"አክሱም" ሲሉም፡ አክሱምን ብቻ እንጂ፡ ኢትዮጵያ በታሪክ አይጨምርም ይሉናል።
ብዙዎቹ ኢትዮጵያውያን ሰው አማኝ ስለሆኑ፡ ፈረንጅ የሚለውን እንደራሳቸው እየመሰላቸው በደግነት ስለሚቀበሉ ነው እንጂ፡ ትኩር ብለው ቢያዳምጧቸው ኖሮ ያለባቸውን ስድብ ማንም ሰሚ እንደማይችለው ያውቁ ነበር። ለነገሩ ኢትዮጵያውያን ፈረንጅ የሚለውን ብዙም አለመከታተላቸው መልካም ሳይሆን አይቀርም። ሰዳቢን ቢከታተሉት ትርፉ ብስጭት ነው። ስለዚህ የፈረንጆቹን ዲስኩር ትተን የራሳችን ስንመረምር ኢትዮጵያ ዕጹብ ድንቅ የሥራ ድርሻ እንዳላት እናያለን።
ኢትዮጵያ የፍጥረታት ሁሉ በኩር ናት፥ ቋንቋዋና ፊደሏም እንዲሁ ከማናቸውም ሀገሮች ቋንቋና ፊደል በፊት በኩር ነው። የኢትዮጵያ ጥንታዊ ክብሯ በቅዱሳት መጽሓፍት ዓምድ ይዞ ይገኛል። ነገር ግን ቅዱስ መጽሐፍና ጥንታውያኑ የታሪክ ጸሓፊዎች የጻፉት ተሰርዞ፡ አዲሱን ወንጌል፡ የአውሮፓ ሰዎች፡ ለሀገር ልማት ማስፋፊያ፥ ለመንግሥታቸው መጠቀሚያ ለማድረግ ወደ አፍሪካ መምጣት ከጀመሩ ወዲህ የተጻፈው እየገነነ በመሄዱ፡ የጸሓፊውን ብዛት ስንመለከተውና፡ የተቀባዩን ማድነቅና ማሞጋገስ ባየነው ጊዜ እጅግ ያሳዝናል ያሳፍራልም። ይህንን የሃሰት ታሪካቸውንም፡ የኢትዮዽያ ልጆች እየተቀበሉ ለመጭው ትውልድ በጽሑፍ ሲያስተላልፉ መኖራቸው ደግሞ የባሰ ያሳምማል ።
ኢትዮጵያዊነት ታላቅ ክብር ነው !
የካቲት ፳፮ ቀን ፣ ፳፻፰ ዓ/ም
No comments:
Post a Comment