EAR

አዲስ ነገር

Friday, 1 January 2016

ቲያንሺ - ባለ በጎ ወይስ ባለ ድብቅ አላማ ድርጅት ?


ዘርአዳዊት -ኢትዮጵያ



የእጄ ስልክ ይጠራል ፡ አነሳሁት ደዋዩ በቅርብ የማውቀው ሰው ነበር። ለጥቂት ጊዜ ስለ ጤንነታችንና ቤተሰብ ጉዳይ ካወራን በኋላ የደወለበትን ምክንያት መናገር ጀመረ። ቅዳሜ መጋቢት 17/2007 በኢድናሞል የፊልም አዳራሽ መቐለ የቲያንሺ ስብሰባ እንዳለና ስብሰባውን እንድካፈል እንደጋበዘኝ ነገረኝ። ስለ ትያንሺ የቡድን ድርጅት በራሪ የሆኑ ወሬዎች እንጂ የተሟላና በቂ የሆነ መረጃ ስላልነበረኝ ስብሰባው ላይ ተገኝቼ በመጠኑም ቢሆን ለማወቅ በመፈለጌ ስብሰባው ላይ በተገለጸው ቀን ለመገኝት አመራው።

የትያንሺ ስብሰባ የሚካሄድበት ኢድናሞል ሲኒማ - መቐለ ከተማ ሁለት ተኩል ሰዓት ደረስኩኝ። የጋበዘኝ ሰው አግኝቸው ሰላምታ ከተለዋወጥን  በኋላ የመግብያ ትኬት እንደቆረጠና መግባት እንደምንችል ነግሮኝ ወደ አዳራሹ ለመግባት ወረፋ ያዛን ። ወደ ውስጥ ለመግባት ሰልፋ ከያዙት ሰዎች መካከል አብዛኛዎቹ በእጃቸው መጽሓፍ የያዙና ብሩህ የሆነ ፊት የሚታይባቸው ነበሩ። የያዝዋቸው መጻሕፍት ምን እንደሆኑ ለማወቅ ባደረኩት ጥረትም ሁሉም በሚባል መልኩ ለለውጥ አነቃቂ የሆኑ የሰነ ልቦናና የሳይነስ መጻሕፍት ነበሩ። እኔ ብቻ ለዚህ ስብሰባ እንግዳ እንደሆንኩኝ ሌሎቹ ብዙ ጊዜ እንደተሳተፉም ተገነዘብኩኝ።

ተራችን ደርሶ ወደ አዳራሹ ገባን። ሁሉም ሰው ቦታው ከያዘ በኋላ የመድረኩ  መሪ አነቃቂ የሆኑ ንግግሮች በማድረግ ወደ የዕለቱ ተናጋሪ (አስተማሪ ብለው ይቀለኛል) የሆነው ሰው መድረኩ ለቀቀ። መድረኩ የተረከበው ሰው አብዛኛዎቹ ታዳሚዎች እንደሚያውቁትና አዲስ ለመጣን ሰዎች ግን ተዋውቆን ዛሬ አነቃቂ የሆነ ትምህርት እንደሚሰጥና በቀጣይ ሳምንት የትያንሺ ድርጅት አባል የሆነውና ከዝቅተኛ ኑሮ ተነስቶ ሚልየነር የሆነ ሰው መጥቶ እንዴት ራሳችንን መለወጥ እንዳለብን ከአዲስ አበባ በመምጣት እንደሚያስተምረን ገለጸ። አሁንም አብዛኛው ሰው በቀጣይ ሳምንት የሚመጣን ሰው ያውቁት ነበርና አዳራሹ በጭሆትና ጭንጨባ ተናጋ። የሰዎቹ የለውጥ መንፈስም ገረመኝ።

መድረኩ የተቆጣጠረው መሪ መግብያ እንዲሆን ብሎ የተናገራቸው ነገሮች ግን ትኩረቴን ያዙት። ትያንሺ የውጭ ድርጅት እንደሆነና ለሰው ልጆች የተመቻቸና የሃብት ክምችት ያለበት የጤና ዋስትና ለመፍጠር የሚስራ መሆኑ ገለጸ። እኔም ወደዚህ ስብሰባ ከመምጣቴ በፊት የነበረኝን ጥርጣሬ ትያንሺ የውጭ ድርጅት መሆኑ ስሰማ ሰዉየው የሚናገራቸው ነገሮች በትኩረት ማድመጥና መከታተል ጀመርኩኝ። በዕለቱ ያስተማራቸው አነቃቂ ነገሮች ግን ከዚ በፊት በተወሰኑ መጻሕፍቶች የማውቃቸው ስለ ነበሩ ትኩረቴ አልያዙትም።

ስብሰባው ተጨርሶ ለቀጣይ ሳምንት ቀጠሮ ይዘን ከአዳራሹ ከወጣን በኋላ የጋበዘኝ ሰው በፈገግታ ተሞልቶ ስብሰባው እንዴት እንደነበር ጠየቀኝ። ጥሩ እንደነበርና ግን ብዙ ጥያቄዎች እንዳሉኝ ገልጬለት ተለያየን። ከዚህ መልስ ነበር ስለ ትያንሺ የቡድን ድርጅት በዓለም አቀፍ የመረጃ መረብ (internet) በመግባት የተወሰኑ መረጃዎች ለመሰብሰብ የቻልኩት።

የድርጅቱ መስራችና ባለቤት ዶክተር ሊጂንዩዋን ይባላል። እ.ጎ.አ በ1998 ነበር የመሰረተው። በሀገረ ቻይና መሰረቱ ያደረገ  ሲሆን በዋናነት የጤና ደህንነት ንግድ ፣ቱሪዝምና  ተያያዥ በሆኑ በዓለም አቀፍ ደረጃ (አንዷ ኢትዮጵያናት ናት) ትኩረት አድርጎ እንደሚሰራ ነው። ድርጅቱ በከፍተኛ ሁኔታ ትኩረት ያደረገው በሚያመርታችው መድሃኒቶችና ይህንን መድሃኒት በማከፋፈል በተዋረድ የተዋቀረው አሰራር አከፋፋይ የሆኑ ግለ ሰቦች ባከፋፈሉት ወይም በሸጡት መጣን ተጠቃሚ የሚሆኑበት አሰራር ነው። በግሌ እንደገባኝም የድርጅቱ ህልውና በዚህ አሰራር ጥገኛ የሆነ ነው። አባላት ማብዛትም ዋነኛው ስራው ነው። እኔው የጋበዘኝ ሰውም ይህንን አላማ ለማስፈጸም ነበር። በዚህ ምክንያትም ሰውየው ስለ ድርጁቱ አዋጭነትና ጠቃሚነት በተለያዩ መንገዶች ሊነግረኝና ሊያሳምነኝ ብዙ የለፋው።vሆኖም በውጭ ድርጅቶች የሚሰሩ አብዛኛዎቹ ሴራዎች በትንሽም ቢሆን ግንዛቤ ስለ ነበረኝ የሚነግረኝ ሁሉ አሜን ብሎ መቀበል አልሆነልኝም። በተቃራኒው ስለ ድርጁቱ በጥልቅ ለማወቅ ፈለኩኝ እንጂ። ወዳጄ እንደነገረኝና በግሌም ባጠናሁት ድርጁቱ የሚያሰራጫቸው መድሃኒቶች ተፈጥራዊ የሆኑና ምንም የጎንዮሽ ጉዳት እንደሌላቸው ነው። እንዲያዉም ፈዋሽነታቸው የፈጠነ እንደሆነ ነው።

ይህንን ሁሉ ይዤ ነበር ከሳምንት በኋላ ዛሬ የተደረገው ስብሰባ የተካፈልኩት። ባለፈው ሳምንት ከተካፈልኩት ስብሰባና ወዳጄ ከነገረኝ መረጃዎች እንደተገነዘብኩት የድርጅቱ አላማ ገንዘብና ገንዘብ ብቻ እንደሆነ ነው። ይህንን አውቄ ነበር ከአዲስ አበባ ከመጣና ከትንሽ ተነስቶ እነዚህ መድሃኒቶች በመሸጥ ሚልየነር የሆነ ሰው የሚሰጠው የተሞክሮ ትምህርት የተጀመረው። ሰውየው ያለፈውን ታሪኩ ከዘረዘረ በኋላ አዳዲስ አባላት መሆን ለምንፈልግ ሰዎች ምንም አይነት የሃይማኖት ይሁን የሌላ ነገር እንቅፋት እንዳይገጥመን ራሱ ሃይማኖተኛ እንደሆነና ማንም ሰው ከአባልነት እንዳይቀርባቸው በሚመስል ሁኔታ ሲሰብክ የነበረው። ምክንያቱም አላማችው ገንዘብ ነውና። ብዙ አባላትን በማፍራት ጥቂት ቁንጮ ሰዎች ብቻ ሃብት የሚሰበሱብበት አሰራር በመሆኑ ብዙ አባል ማፍራት መጠቀምያ መሆኑ ግልጽ ይሆናል። በጣም ከገረመኝ ነገር የትያንሺ ድርጅት መስራች ዶክተር ሊጂንዩዋን  በፕሮጀክተር ስክሪን ምስሉ ሲያሳዩን በጣም ከፍተኛ ክብደትና የተበላሸ የሰውነት ቅርፅ ያለው ሰው ነው። በሚያስተላልፉት መልዕክትና በሚሸጡት መድሃኒቶች ግን መድሃኒቱ የሰውነት ቅርጽ ለመጠበቅና ክብደት ለመቀነስ እንደሚረዳ ነበር። ሰላቢ  እጆች በመድሃኒት ሰበብ የሚሰሩት ሴራ የተገነዘበ ሰው መጠርጠር ደግ መሆኑ ያውቃል። ታድያ ይህ ድርጅት ባለ በጎ ወይስ ባለ ድብቅ አላማ  ?  

ቅዳሜ መጋቢት 24, 2007 ዓመተ ምሕረት



ቅዳሜ መጋቢት 24, 2007 ዓመተ ምሕረት

No comments: