በታምራት ነገራ
ልክ የዛሬ 81 ዓመት እንደአውሮፓውያን አቆጣጠር በጃንዋሪ 6 1936 ግርማዊ ቀዳማዊ ሀይለስላሴ በታዋቂው የታይም መጽሄት የዓመቱ ሰው ተብለው ተሰይመው ነበር፡፡ መጽሄቶች ከፍተኛ ተጽእኖ በነበራቸው የቀድሞው ክፍለ ዘመን አይደለም የመጽሄቶች ሽያጭ እና ፖለቲካዊ ሚና በተንኮታኮተበት ዘንድሮም እንኳን የታይም መጽሄት የዓመቱ ምርጥ ሰው መባል፤ እጅግ አነጋጋሪ፤ አወዛጋቢ የሚመኙት፤ የሚጓጉለት፤ የሚሻሙለት ግንባር የሆነ ስፍራ ነው፡፡
በተለይም እንደ ግርማዊነታቸው በመልካም ስም የታይም መጽሄት የዓመቱ ሰው መባል እንደ እንቁ ውድ የሆነ ዝና ነው፡፡ ግርማዊነታቸው የዛሬ 81 አመት የታይም መጽሄትን ክብር ያጎናጸፋቸው ከፋሺዝም ጋር የነበራቸው ግብ ግብ ነበር፡፡ የመጽሄቱ እሳቸውን የዓመቱ ምርጥ ሰው ያላቸው እኤአ 1935 ስለነበራቸው ተጋድሎ ነበር፡፡ በእኤአ ጁን 1936 ደግሞ እስከአሁን ድረስ ተጠቃሽ የሆነላቸውን የሊግ ኦፍ ኔሽንስ ንግግር አደረጉ፡፡
ግርማዊነታቸው በወቅቱ በስደት ዘመናቸው ከፋሺዝም ጋር ከፍተኛ ዲፕሎማሲያዊ ግብ ግብ ላይ ስለነበሩ አይደለም የታይም መጽሔት የአመቱ ሰው መባልን የትኛውንም አይነት መድረክ በቀላሉ እንደማያልፉት መገመት አያዳግትም፡፡ ግርማዊነታቸው በታይም መጽሄት የዓመቱ ሰው ሽፋንም ማግኘት ተጠቃሚው እሳቸው ብቻ ሳይሆኑ መላው የጥቁር ሕዝብ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ለኢትዮጵያም ስሟ በመልካም በዓለም ሚዲያ ከተነሳባቸው አጋጣሚዎች አንዱ ነው፡፡
የትውልድ ጥያቄዎች
ትውልዳችን ዘንድሮ ላይ ቆሞ ታይም ስለግርማዊነታቸው ምን እንዳለ መልሶ ከመከለስ ባሻገር ሌላ የቤት ስራ ሳይጠብቀው አይቀርም፡፡ ከቀን ወደቀን የኢትዮጵያንም ሆነ የኢትዮጲያውያንን ስም በወሳኙ የዲፕሎማሲ መድረክ በመልካም ስም እና በልቀት ለማስነገር እየከበደ ከመጣ ግን እጅጉን ሰነባበተ፡፡
የኢትዮጵያን ውጭጉዳይ ሚኒስትር ወይንም የሚያስተዳድራቸውን የኢትዮጵያ ኤምባሲዎቻችን ድረ ገጽ መለስ ብሎ ለቃኘ አሁን ያለው የኢትዮጵያ መንግስት ስለዲፕሎማሲ ያለው ግንዛቤ እና ልህቀት ግርማዊነታቸው እና በአከባቢያቸው የነበረው ቢሮክራሲ ከነበረው ግንዛቤ በእጅጉ የኮሰሰ እንደነበር ለማወቅ ይቻላል፡፡
ግርማዊነታቸው በስደት በእነ ሎሬንዞ ትዕዛዝ ያንቀሳቀሱት የዲፕሎማሲ መዋቅር ሙሉ መንግስት መዋቅር ይዞ ከሚንቀሳቀሰው ወቅታዊው የኢትዮጲያ መንግስት በብቃት ያነሰ መሆኑ ሁሉንም ኢትዮጵያዊ ሊያሳዝነውም ሊያሳስበውም የሚገባ የጋራ ኪሳራ ነው፡፡ የግርማዊነታቸው ስኬት ለአገራችን የጋራ ብስራት እንደሆነው ሁሉ የገዢው ፓርቲ ተቃዋሚ ብንሆንም በኢትዮጵያ መንግስት በኩል የሚያደርሰው ኪሳራም የጋራ ወራሽ ነን፡፡
ግርማዊነታቸው በዲፕሎማሲ እንዲልቁ ያስቻሏቸው ምን ምክንያቶች ነበሩ? ምን አይነት እርምጃዎችን ወስደው ምን አይነት ውጤቶችን አግኝተዋል የሚሉት ጥያቄዎች ዛሬም ለአገራችን በጣም ወሳኝ ጥያቄዎች ናቸው ባይ ነኝ ፡፡ ታሪክን መከለስ ብቻ ሳይሆን ከታሪክ ለዛሬ ምን ትምህርት ይገኛል ማለት የተሻለ ፋይዳ አለው፡፡ የዛሬዋ ኢትዮጵያ ከ81 ዓመታት በፊት የነበረችውን ኢትዮጵያ አትመስልም ስለዚህ ምንም ከጥንታዊት ኢትዮጵያ ልንማር አንችልም እናም ወደኋላ መመልከት ተገቢ አይደለም ከሚል ሰሞነኛ መከራከሪያ መሳይ ሽባ አመክንዮ ጋር መነጋገር ድንጋይ ላይ ውሀ እንደማፍሰስ ስለሆነ በሱ ላይ በማተኮር ጊዜም ስፍራም አልፈጅም፡፡
ዲፕሎማሲ መሰረት ይፈልጋል
ግርማዊነታቸው እኤአ 1936 በታይም መጽሄት ላይ ላገኙት የመታወቅ ክብር ወሳኙን ዲፕሎማሲያዊ መሰረት የጣሉት እኤአ 1924 በአውሮፓ እና መካከለኛው ምስራቅ ባደረጉት ጉዞ ላይ ነው ማለት ይቻላል፡፡ በወቅቱ አልጋ ወራሽ የነበሩት ቀዳማዊ ሓይለ ሥላሴ ከአገራቸው ውጪ ጉብኝት በማድረግ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ልዑል እና አገረ ገዢ መሆናቸውን እሳቸውም ተቀባዮቻቸውም አሳምረው ያውቁ ነበር፡፡ ይህም ከምዕራባውያን ጋር በምዕራባውያን ምድር የሚደረግ ግንኙነት እንደመሆኑ በመጀመሪያ ትውውቅ ወቅት የሚፈጠርን በጎ ስሜት (First Impression) አስፈላጊነት ግርማዊነታቸው በሚገባ ተገንዝበውት ነበር፡፡
በወቅቱ የግርማዊነታቸው ኦፊሴልያዊ የጉብኝት ምክንያት ኢትዮጵያ በሊግ ኦፍ ኔሽንስ ለመሳተፍ ስትጠይቅ ለተደረገላት እገዛ ምስጋና እንደሆነ ተነግሯል፡፡ የግርማዊነታቸውን ታሪክ በሰፊው ካጠኑት ምሁራን አንዱ የሆኑት ሀሮልድ ማርከስ ደግሞ የግርማዊነታቸው የጉዞ ምክንያት ለኢትዮጲያ የባሕር በር ከፈረንሳይ ለማስገኘትም ጭምር እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡ በሜይ 17 1924 ስለግርማዊነታቸው ጉዞ የዘገበው ኒውዮርክ ታይምስ ደግሞ በዚህ የአውሮፓ ጉብኝት ግርማዊነታቸው የፈለጉት ምእራባውያኑን እሳቸውንም ሆነ አገራቸውን እንደ እኩያ እና ነጻ አገር እንዲያዩአቸው በአይምሮ ጨዋታ በልጠው ለመገኘት እንደፈለጉ ያትታል፡፡
የባሕር በር ጥያቄአቸው በፈረንሳይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ውድቅ ሆነባቸው፡፡ እራሳቸውንም ሆነ የአገራቸውን ግርማ እና ዝና ለማንሰራፋት ያደረጉት ጥረት ግን እጅጉን የተሳካ የዲፕሎማሲ ድል ነበር፡፡ ይህ የአውሮፓ መንግስት ባለስልጣናትንም ሆነ የአውሮፓ ዜጎች ላይ ያነጣጠረ ሁለትዮሽ የዲፕሎማሲ ግንባር የተሳካ እንዲሆን ግርማዊነታቸው የተለያዩ ዘዴዎችን ተጠቅመዋል፡፡
ግርማዊ አጀብ
ግርማዊነታቸውን አጅበው ወደ አውሮፓ የተጓዙት መሳፍንት፤ መኳንንት እና ባላባቶች እነ ራስ ስዩም መንገሻ፤ ራስ ሀይሉ ተክለሀይማኖት፤ ራስ ሙሉጌታ ይገዙ ፤ራስ መኮንን እንዳልካቸው እና ብላቴን ጌታ ሕሩይ ወልደስላሴ ልክ እንደ ግርማዊነታቸው በማንም ፊት አንገታቸውን ቀና ማድረግ የሚችሉ የራሳቸው ስብእና ያላቸው ናቸው፡፡ እነዚህም ሰዎች በአነጋገርም ሆነ በአቋቋም ለግርማዊነታቸው ተጨማሪ ሞገስ ማሰጠት የሚያስችሉ ነበሩ፡፡ ይህን የሚያሳየን አንደኛው አጋጣሚ በእንግሊዙ ጉዞ ወቅት የግርማዊነታቸውን እና ልዑካኑን ገጠመኝ ስንመለከት ነው፡፡
በግርማዊ ጉብኝት ወቅት ቤኪንግሀም ቤተመንግስት ግርማዊነታቸው በእንግሊዙ ንጉስ ጆርጅ አምስተኛ አቀባበል ተደረገላቸው፡፡ በዚህ ወቅት ግርማዊነታቸውን ያጀቡት የራስ ሀይሉ ተክለሐይማኖትን ልዑልነት የሰሙት ጆርጅ አምስተኛ በአስተርጓሚ በኩል ራስ ሐይሉ እንግሊዘኛ ይችሉ እንደው ይጠይቃሉ አስተርጓሚም ራስ ሀይሉ እንግሊዘኛ እንደማያውቁ ይናገራሉ፡፡ እንግዲያው ራስ ሀይሉ ፈረንሳይኛ ወይም ጀርመንኛ ይችሉ እንደው ይጠይቃሉ፡፡ አሁንም መልሱ ራስ ሀይሉ የተጠየቁትን ቋንቋዎች እንደማይችሉ ሆነ፡፡ በመልሱ የተበሳጩት ጆርጅ አምስተኛ ለአስተርጓሚው ራስ ሀይሉን ደንቆሮ ነህ በልልኝ ይላሉ፡፡
ራስ ሀይሉ ተክለ ሐይማኖት ምልልሱን በጥሞና ካደመጡ በኋላ አስተርጓሚውን በል ግርማዊነታቸውጆርጅ አምስተኛ አማርኛ ይችሉ እንደው ጠይቅልኝ ይላሉ፡፡ መልሱም ጆርጅ አምስተኛ አማርኛ እንደማይችሉ ሆነ፡፡ እንግዲያው ትግርኛ ወይንም ጉራግኛ እንደሚችሉ ጠይቅልኝ ይላሉ፡፡ አሁንም መልሱ ጆርጅ አምስተኛ ትግርኛም ሆነ ጉራግኛ አለመቻላቸው ሆነ፡፡ ይሄኔ ራስ ሀይሉ ቀብረር ጀነን ብለው እሳቸውም እንደኔ ደንቆሮ እንደሆኑ ንገርልኝ አሉ፡፡ ምላሹን የሰሙት ጆርጅ አምስተኛም ከትከት ብለው ሳቁ ራስ ሀይሉንም ወደዷቸው በዛውም አመት ኦርደር ኦፍ ዘ ብሪቲሽ ኢምፓየር የተሰኘውንየእንግሊዝ የክብር ማዕረግ ሸለሟቸው፡፡ ራስ ሐይሉ ወደኋላ ላይ በባንዳነት አሳፋሪ ታሪክ ቢኖራቸውም በዚህ ወሳኝ ዲፕሎማሲያዊ መድረክ እራሳቸውንም ግርማዊነታቸውንም ለማስከበር የሚበቃ ሚና ተጫውተዋል ማለት ይቻላል፡፡ ከራስ ሐይሉ በተጨማሪ ከግርማዊነታቸው ጋር ወደ አውሮፓ እና መካከለኛው ምስራቅ የተጓዙት እነ ራስ ሙሉጌታ ይገዙ በአድዋው ላይ ከነበራቸው የተዋጊነት ተሳትፎ የተነሳ የአውሮፓውያንን ልብ ለማማለል አስችለው ነበር፡፡ ግርማዊነታቸውም ሆነ አጃቢዎቻቸውም በአውሮፓ ባደረጉት ጉዞ ሁሉ ሊያያቸው እና ሊቀበላቸው የወጣውን ሰው ሁሉ ከመጤፍ ባለመቁጠር ተንቀባረው ይታዩም ነበር፡፡ ተቀባዮቻቸው ላይ ያሳዩት ጅንንነትም እጅጉኑ ተወዳጅ አድርጓቸው እንደነበር እና ውጤታማ እንደሆነ ኒውዮርክ ታይምስ ዘግቧል፡፡
ስጦታ የዲፕሎማሲ ቁልፍ
ግርማዊነታቸው በዚህ ጉዞ ላይ የአውሮፓውያንን ልብ ለማማለል የተጠቀሙት ሌላው ዲፕሎማሲያዊ መሳሪያ ስጦታ ነው፡፡ ግርማዊነታቸው ለፈረንሳዩ ፕሬዘዳንት አሌክሳንደር ሚሌራንድ፤ ለፈረንሳዩ ጠቅላይ ሚኒስቴር ሬሞን ፔንኬር፤ ለእንግሊዙ ንጉስ ግርማዊ ጆርጅ አምስተኛ እና ለፈረንሳዩ የዙዎሎጂ ጋርደን ይዘዋቸው የመጡትን አንበሶች በስጦታነት አበርክተዋል፡፡
ስጦታዎቹም ግርማዊነታቸውን በተቀበሏቸው ዘንድ ከፍተኛ ፍላጎት እና አድናቆትም መቀስቀስ ችለው ነበር፡፡ በግርማዊነታቸው የአንበሶች ስጦታ የተደሰተው የእንግሊዝ መንግስትም በመቅደላ ጦርነት ወቅት ተወስደው ከነበሩት የኢትዮጵያ ንብረቶች መካከል የአፄ ቴዎድሮስን ዘውድ ግርማዊነታቸው ለንግስት ዘውዲቱ ይዘው እንዲሄዱ መልሶ አስረክቧል፡፡ በአጠቃላይ ጉዞው የሚዲያ የሕዝብ ለሕዝብ ዲፕሎማሲ (Public Diplomacy) ድል ነበር፡፡
በዚህ ዲፕሎማሲያዊ ድል የተገኘው ሌላኛው ውጤት የተመዘገበው ደግሞ ከግርማዊነታቸው የአውሮፓ ጉብኝት ስድስት አመት በኋላ ነው፡፡ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ኖቬምበር 3 1930 የታይም መጽሄት የግርማዊነታቸውን ስርአተ ንግስና ተከትሎ የፊት ገጹ ላይ ሰፊ ሽፋን ሰጥቶ ዘገባቸው፡፡ ግርማዊነታቸው በ1924 የተሳካ ዘመቻ ባያደርጉ ኖሮ በ1930ው የታይም መጽሄት ስርአተ ንግስናቸውን አይዘግብላቸውም ነበር፡፡ ታይም መጽሄት በ1930 ስርአተ ንግስናቸውን በሚገባ ባይዘግብ ኖሮ በ1936 የዓመቱ ምርጥ ሰው አይላቸውም ነበር፡፡ የዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ዝም ብለው ከሜዳ ተነስተው አይሾሙም እውቅና አይሰጡም አይሸልሙም፡፡ ተከታታይ የሆነ ከፍተኛ የሕዝብ ግንኙነት ስራ ይጠይቃል፡፡
ግርማዊነታቸው እንዲህ አይነት የተራቀቀ ዲፕሎማሲያዊ ክህሎት እና እይታ እንዲያዳብሩ አስተዳደጋቸው እራሱ አስተዋጽኦ ማበርከቱ አያጠራጥርም፡፡ አባታቸው ራስ መኮንን ወልደሚካኤል ጉዲሳ እኤአ 1902 የእንግሊዙን ንጉስ ግርማዊ ኤድዋርድ ሰባተኛ የንግስ ስርአት ለመሳተፍ ኢትዮጵያን ወክለው እንደሄዱ ይታወቃል፡፡ በዚህ ታሪካዊ ጉዞአቸውም ወቅት ራስ መኮንን ከአጃቢዎቻቸው ጋር የተነሱት እጅግ ግሩም የሆነ ፎቶ በዓለም የፋሽን ታሪክ ውስጥ ድንቅ ከተሰኙ ወቅቶች አንዱ እንደሆነ የላፕሀም ኳርተርሊ የተሰኘው ሕትመት በቅጽ 8 ቁጥር 4 ስለፋሽን ባቀረበው ልዩ ዘገባ ላይ ተመዝግቧል፡፡
ግርማዊነታቸውም ሆነ ኢትዮጵያ በተለያዩ የዲፕሎማሲያዊ መስኮች ያገኘችው ድል መልሶ የማይደገምበት ምክንያት የለም፡፡ ነገር ግን ይህ ድል ዝም ብሎ በመፈክር እና በጩኅት አይመጣም፡፡ ግልጽ ብሔራዊ ግብ፤ እራስን ማወቅ፤ እራስን መሆን፤ በእራስ መተማመን፤ ብቃት ያላቸውን ባለሙያዎች ማፍራት፤ ባለሙያዎችንም መስማት ይጠይቃል፡፡
No comments:
Post a Comment