✍ ዘርአዳዊት ዘ-ኢትዮጵያ
ሉቃስ 17፣ 1-2 ፦ “ለደቀ መዛሙርቱም እንዲህ አለ፦ መሰናክል ግድ ሳይመጣ አይቀርም፥ ነገር ግን መሰናክሉን ለሚያመጣው ወዮለት፤ ከእነዚህ ከታናናሾች አንዱን ከማሰናከል ይልቅ የወፍጮ ድንጋይ በአንገቱ ታስሮ ወደ ባሕር ቢጣል ይጠቅመው ነበር።”
ሲጀመር ይህን ጥያቄ መጠየቁ ታላቅ ሞኝነት ነው፣ ሁለተኛ ለመመለስ የምንገደድበት ጊዜ ላይ መድረሳችን ደግሞ ዘመኑ ምን ዓይነት እንደሆነ ያሳያል፡፡ ስለዚህ ይህ የዘመኑን ክፍተት ለመሙላት ሲባል ለመጻፍ እንገደዳለን፡፡
መጀመርያ በክርስቶስ አምላክነት የሚያምን ሰዶምና ገሞራን ያጠፋ አምላክ መሆኑን ስለሚረዳ ይህ የሞኝነት ጥያቄን አያነሳም ነበር፡፡ ከዚህም በመቀጠል ግን ክርስቶስ ይህ በሕግጋት የተከለከለውን ተግባር መፈጸም እንደሌለበትም አስተምሯል፡፡
በቀጥታ አላስተማረም የሚሉት ባይባል እንኳ ለምሳሌ “ጊታር አታግቡ” “ዶልፊን አታግቡ” “አሻንጉሊት አታግቡ” “ሕጻናት አታባልጉ” አልተባለም ብለን እነዚህን ድርጊቶች ልንከተል ነው? እነዚህን ድርጊቶች ያደረጉትስ ትክክል ናቸው ልንል ነው? አንልም፡፡
ማቴ. 19፣ 4-6 እንዲህ ይላል፦
“እርሱ ግን መልሶ እንዲህ አለ፦ ፈጣሪ በመጀመሪያ ወንድና ሴት አደረጋቸው፥ አለም። ስለዚህ ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል፥ ከሚስቱም ጋር ይተባበራል፥ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ የሚለውን ቃል አላነበባችሁምን?
“ስለዚህ አንድ ሥጋ ናቸው እንጂ ወደ ፊት ሁለት አይደሉም። እግዚአብሔር ያጣመረውን እንግዲህ ሰው አይለየው።”
ክርስቶስ እንዲህ ሲል አንድ ወንድ ለአንዲት ሴት፣ አንዲት ሴትም ለአንድ ወንድ መሆኗን ይነግረናል፡፡ በዚህም በየትኛውም በኩል ከአንድ በላይ ጋብቻ እንደማይፈቅድ ይነግረናል፡፡ በተጨማሪም ወንድና ሴት እንጂ ከየትኛውም በኩል ተመሳሳይ ጾታ ያለቸው ሰዶማዊ ተግባር ውስጥ መግባት እንደሌለባቸው ይነግረናል፡፡
ሉቃስ 17፣ 28-30 ፦ “እንዲሁ በሎጥ ዘመን እንደ ሆነ፤ ይበሉ ይጠጡም ይገዙም ይሸጡም ይተክሉም ቤትም ይሠሩ ነበር፤ ሎጥ ከሰዶም በወጣበት ቀን ግን ከሰማይ እሳትና ዲን ዘነበ ሁሉንም አጠፋ። የሰው ልጅ በሚገለጥበት ቀን እንዲሁ ይሆናል።”
ይህ ከላይ የተቀመጠው ጥቅስ ደግሞ ክርስቶስ በቀጥታ ስለመጨረሻ ዘመን ጠይቀውት እንዴት በሰዶም ጊዜ እንደነበረው እንደሚሆንና በዚሁ ኃጥያታቸውም እንደሚጠፉ ይነግረናል፡፡
ይህ በቀጥታ ስለተናገረው ለማስቀመጥ ያህል ነው፡፡ ከርሱ በፊት ስለተገለጠው ሕግ፣ ሰዶምና ጎመራን ስለበላው ሕግ ደግሞ በማቴ. 5፣ 17 ላይ እንዲህ ይላል፦ “እኔ ሕግንና ነቢያትን ለመሻር የመጣሁ አይምሰላችሁ፤ ልፈጽም እንጂ ለመሻር አልመጣሁም።”
ለመሆኑ ሕግና ነቢያት ስለ ግብረሰዶም ምን ይላሉ? ከስር እንመልከታቸው፡፡
“ማናቸውም ሰው ከሴት ጋር እንደሚተኛ ከወንድ ጋር ቢተኛ ሁለቱ ጸያፍ ነገር አድርገዋል ፈጽመው ይገደሉ ደማቸው በላያቸው ነው።” --- ዘሌዋውያን 20፣ 13፡፡
“ከሴትም ጋር እንደምትተኛ ከወንድ ጋር አትተኛ ጸያፍ ነገር ነውና። እንዳትረክስባትም ከእንሰሳ ጋር አትተኛ ሴት ከእርሱ ጋር ትተኛ ዘንድ በእንስሳ ፊት አትቁም የተጠላ ነገር ነውና። በእነዚህ ሁሉ ከፊታችሁ የማሳድዳቸው አሕዛብ ረክሰዋልና በእነዚህ ነገሮች ሁሉ አትርከሱ። ምድሪቱም ረከሰች ስለዚህ ኃጢአትዋን በእርስዋ ላይ እመልሳለሁ፥ ምድሪቱም የሚኖሩባትን ሰዎች ትተፋለች።”
--- ዘሌዋውያን 18፣ 22-25፡፡
“ስለዚህ እግዚአብሔር ለሚያስነውር ምኞት አሳልፎ ሰጣቸው፤ ሴቶቻቸውም ለባሕርያቸው የሚገባውን ሥራ ለባሕርያቸው በማይገባው ለወጡ፤ እንዲሁም ወንዶች ደግሞ ለባሕርያቸው የሚገባውን ሴቶችን መገናኘት ትተው እርስ በርሳቸው በፍትወታቸው ተቃጠሉ፤ ወንዶችም በወንዶች ነውር አድርገው በስሕተታቸው የሚገባውን ብድራት በራሳቸው ተቀበሉ።”
--- ወደ ሮሜ 1፣ 26-27፡፡
“ወይስ ዓመፀኞች የእግዚአብሔርን መንግሥት እንዳይወርሱ አታውቁምን? አትሳቱ፤ ሴሰኞች ቢሆን ወይም ጣዖትን የሚያመልኩ ወይም አመንዝሮች ወይም ቀላጮች ወይም ከወንድ ጋር ዝሙት የሚሠሩ. . .”
---1ኛ ቆሮ. 6፣ 9፡፡
“ይኸውም፥ ለበደለኞችና ለማይታዘዙ፥ ለዓመጸኞችና ለኃጢአተኞች፥ ቅድስና ለሌላቸውና ለርኵሳን፥ አባትና እናትን ለሚገድሉ፥ ለነፍሰ ገዳዮችና ለሴሰኞች፥ ከወንድ ጋርም ለሚተኙ፥ በሰዎችም ለሚነግዱ፥ ለውሸተኞችም በውሸትም ለሚምሉ፥ የብሩክ እግዚአብሔርንም ክብር እንደሚገልጥ ለእኔ አደራ እንደ ተሰጠኝ ወንጌል የሆነውን ደኅና ትምህርት ለሚቃወም ለሌላ ነገር ሁሉ ሕግ እንደ ተሰራ እንጂ ለጻድቅ እንዳልተሰራ ሲያውቅ ነው።” --- 1 ጢሞ. 1፣ 9-11፡፡
አዎ! ክርስቶስ ሕግን ሊሽር አልመጣም ሕግም አጥብቆ የሚያወግዘው ድርጊት ነው፡፡
No comments:
Post a Comment